አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ።
“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በተለያዩ ከተሞች ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የተገኙት ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) መንግሥት የህዝብን ጥያቄዎችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ቁርጠኝነት የህብረተሰቡ ድጋፍ ከታከለበት ጥያቄዎችን አንድ በአንድ እየተፈቱ የሚሄዱ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እውነተኛ የሆነ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጎለብትና እንዲፀና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተው፤ ብልፅግናን ፓርቲ አሰባሳቢና ገዥ ትርክትን ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሀብት መፍጠር ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ተፈጥሮ ያደለንን ፀጋ በአግባቡ ተጠቅመን የከተሞችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሌት ከቀን መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለትውልድ ዕዳ ሳይሆን ምንዳን እና የተደላደለ ምቹ ሀገርን ለማስረከብ በምናደርገው ሂደት ውስጥ እያንዳንዳችን የራሳችንን ድርሻ መውጣት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጽናት ለማለፍ በትብብርና በውይይት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ መንግስት የህዝቡን አንገብጋቢና መሠረታዊ ጥያቄዎችን ትኩረት ሰጥቶ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎችን በግብዓትነት በመጠቀም የቀጣይ ዕቅድ አካል በማድረግ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሁሉም ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአበበች ኬሻሞ