Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምንመኛትን አፍሪካ ለመፍጠር ለትምህርት የሚመደበውን ሀብት ማሳደግ ይገባል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአጀንዳ 2063 የምንመኛትን አፍሪካ ለመፍጠር በትምህርት ዘርፍ ላይ የሚመደበውን ሀብት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

የአፍሪካ ሕብረት 2024 የትምህርት ዓመት በሚል የተሰየመ ሲሆን “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” የሚለውን መሪ ሀሳብ የማስተዋወቅና ገለፃ የማድረግ መረሃ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።

በመረሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ተወካዮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው በአጀንዳ 2063 የምንመኛትን አፍሪካ ለመፍጠር በትምህርት ዘርፍ ላይ የሚመደበውን ሀብት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የአፍሪካን ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው የእድገት ሽግግር ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት አፍሪካን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ለማድረግ ለትምህርት ትኩረት መስጠት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ሕብረቱ ሁሉንም አቅም በማስተባበር በአህጉሪቱ ጥራት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን ሃላፊነቱን እንደሚወጣም ገልፀዋል።

Exit mobile version