አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ አሁን ከምንጊዜውም በላይ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ ልንጠብቅ ይገባል ሲሉ አሳሰቡ።
ብፁዕ ካርዲናሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ ይህንን ጊዜ ለማለፍ መረዳዳት ያስፈልጋል እኛ ቤት ስንቀመጥ መጠለያ ለሌላቸው እና ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ወገኖችንም ለመርዳት ሁሉም የሚቻለውን ይወጣ ብለዋል።
በኮቪድ 19 ሳቢያ በርካታ የተለመዱ እንቅስቃሴዎች ታግደዋል፥ ማህበራዊ ኑሯችንም ባልተጠበቀ መልኩ ቢቀየርም ፤ጤና ለሰው ልጆች አስፈላጊ ስለሆነ ራሳችንን መጠበቅ ቅንጦት ልናደርገው አይገባም ብለዋል።
አሁን ላይ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መፍትሄን ለማግኘት ብሎም ሊፈጠር የሚችለውንና ለተፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው÷በዚህ ጥረት ውስጥ በመሳተፍ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል ብፁዕ ካርዲናሉ በመግለጫቸው።
ወረርሽኙን ለመግታት በቤታችን ስንቀመጥ የህይወትን ትርጉም የምንመረምርበት አጋጣሚ በማድረግ ለንስሃ፣ ለመለወጥ፣ ለፈጠራ በመጠቀም ልጆች ሳይሰለቹ የሚማሩበትን መንገድ እንፈልግ ነው ያሉት ።
ብፁዕ ካርዲናሉ አያይዘውም ምድር በሰው ልጆች ራስ ወዳድነት ክፉኛ ታማለች ይህንን ልናድን የሚገባን እኛው ነን ብለዋል።
የፊታችን ክረምት 5ቢሊየን ችግኝ እንዲተከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ ህብረተሰቡ ችግኝ እንዲተክልም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም በመጪው ክረምት በተጠራው የችግኝ መትከል መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
በዚህ አመት ከወትሮው በተለየ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ መሰባሰብን፣ በጋራ ሆነን መትከልን የማንችልበት ቢሆንም፤ ርቀታችንን ጠብቀን በጤና ባለሙያዎች የወጡትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ብሎም ራሳችንን ከቫይረሱ ጠብቀን ልንተክል ይገባል ነው ያሉት።
ብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳሳት ፍራንቸስኮ “የሁላችን ቤት” ብለው የሚጠሯትን ምድርን እንድንከባከብ በአደራ ጭምር ተናግረዋል ÷ የአካባቢ እንክብካቤ ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀውን መልዕክታቸውን ዘንድሮም አክብረናል ያሉት ካርዲናሉ ህብረተሰቡ ችግኝ መትከልን በልዩ ክብረ በዓላት ላይም ልማድ ቢያደርግ መልካም ነው ብለዋል።
በሃይማኖት ኢያሱ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

