አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ10 ወራት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
ማዕከሉ ያለበት ደረጃ መገምገሙን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ችግሮች እና ለወሲብ ንግድ የተጋለጡ እህቶች ተሃድሶ በመስጠት መልሶ ለማቋቋም እየተገነባ ያለዉ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ በየዓመቱ እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ የጎዳና ሴቶች ስልጠና በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እና ገቢ እያገኙ እራሳቸውን እንዲችሉ እንደሚያግዝ ነው የተመላከተው፡፡
በውስጡም የተሃድሶ ስልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት ፣ የስነ ልቦና እና ምክር አገልግሎት፣የህክምና ማእከል ፣ ማደሪያ ፣ መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ስፍራዎች መካተታቸው ተመላክቷል፡፡