Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተመድ የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የተባበሩት መንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ሰርዋ ገለጹ።

ሃና ሰርዋ አፍሪካ የሚያጋጥሟትን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በራሷ የመፍታት አቅም ያላት ትልቅ አህጉር መሆኗን አውስተዋል፡፡

አፍሪካ የሚያጋጥሟትን የተለያዩ ተግዳሮቶች በራሷ መፍትሄ ለመስጠት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው÷ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን እሳቤ እውን ለማድረግ ተመድ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2017 በተመድና በአፍሪካ ህብረት መካከል በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ተቋማቸው ከማማከር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አፍሪካን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በአሁን ጊዜ በተለያዩ የአህጉሪቷ ክፍሎች የሚታዩ አለመረጋጋቶች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ የአፍሪካ መሪዎች የህግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትና ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ፍላጎታቸውን በሃይል ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት የዜጎችን እንግልት ከመጨመር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለውም ልዩ መዕክተኛዋ ገልጸዋል።

ችግሮችን በውይይትና በድርድር የመፍታት ባህል እየዳበረ ካልመጣ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አዳጋች እንደሚሆንም ተናግረዋል።

Exit mobile version