አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፈረንጆቹ 2024 የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሆነው ለተመረጡት የሞሪታኒያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ኡልድ አል ጋዙዋኒ የዓመቱ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው የ’እንኳን ደስ አልዎት’ መልካም ምኞት መርሃግብር ዛሬ ተካሄደ።
በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተገኝተዋል፡፡
በወቅቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ኡልድ አል ጋዙዋኒ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ለተደረገላቸው መስተንግዶ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሞሪታኒያው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ኡልድ ኤል-ጋዝዋኒ የ2024 አፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሶማኒ በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በይፋ መረከባቸው ይታወቃል።