አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ተደርጎ እንደሚወሰድ የ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊዎች ገለፁ፡፡
በምግብ ራስን መቻል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን የብራዚል-አፍሪካ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ጃኦ ቦስኮ ሞንቴ (ፕ/ር) አስረድተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ተፅኖዎችን ለመመከት በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህ ጉዳይም የአፍሪካውያን ቀዳሚ ጥረት ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የብራዚል-አፍሪካ ኢንስቲትዩት በግብርናው ዘርፍ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የብራዚል የግብርና ማስታወቂያ ኩባንያ ባለሙያ አሌክሳንደር ትራቦልድ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ እና በዓለም መድረክም እውቅና የተቸረው መሆኑን አንስተዋል፡፡