አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን በማሰናዳት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ሰርታለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ፡፡
በጉባኤው ዙሪያ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ብርቱካን በመግለጫቸው ÷ ከየካቲት 6 እስከ 10 ቀን 2016ዓ.ም የስራ አስፈጻሚዎች እና 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ተስተናግደዋል ብለዋል፡፡
ከጉባኤው አስቀድሞም ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራ መቆየቱን እና በሀገራዊ መንፈስ በጋራ መሰራቱን አምባሳደር ብርቱካን ገልፀዋል።
በዚህም ጉባኤ 31 ሀገራት በመሪዎች ደረጃ፣ 6 ሀገራት በምክትል መሪዎች ደረጃ፣ 7 በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ፣ 2 በሀገራቱ ተወካዮች፣ 1 በኤምባሲ ደረጃ በአጠቃላይም 49 ሀገራት ልዑካን ቡድን በጉባኤው ተካፍለዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪ 14 የዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ከ500 በላይ የውጭ ሚዲያዎች በጉባኤው መሳተፋቸውን አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ የ13 ሀገራት የቀዳማዊት እመቤቶች በ28ኛው የቀዳማዊት እመቤቶች ጉባኤ ላይ መካፈላቸውን ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ÷ ኢትዮጵያ ጉባኤውን በማሰናዳት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ሰርታለች ነው ያሉት።
በሚነሱ አጀንዳዎችም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ስራዎች የተሰሩበት ነው ፤ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ከቋሚ መልዕክተኞች እስከ መሪዎች ጉባኤ ድረስ በትኩረት ተመክሮበታል ነው ያሉት።
በህብረቱ ጉባኤ ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን ማስገምገሟን ገልፀው ፥ በጉባኤው በበጎ አፈጻጸም እንደተገመገመ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻ ንግድ በተመለከተ የሸቀጦች የዋጋ ዝርዝር ታሪፍን ዝርዝር አቅርባ በጉባኤው አጸድቃለች ፤ በዚህም ኢትዮጵያ ዘጠኝ ንግድ መጀመር ከሚችሉ ሀገራት ዝርዝር ተካታለች ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአፍሪካ ሀገራትን የግብርና አፈጻደም በበላይነት የሚከታተሉ እንደመሆኑ የሀገራት ሁኔታና የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ሁኔታ ለጉባኤው ማቅረባቸውን አውስተዋል፡፡
በጉባኤው የአፍሪካን የትምህርት ጥራት ማስጠበቅን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው አፍሪካ በትምህርት ኢንቨስትመንት ላይ ማተኮር እንደሚገባት ሃሳባቸውን ማጋራታቸውን አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶች የተካፈሉበት ይህ ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን ÷ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ አስተዋፅዖ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና ቀርቧል፡፡
በምስክር ስናፍቅ