Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሙስና ወንጀል የተከሰሰው የፍርድ ቤት ዳኛ ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል የተከሰሰው የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዳኛና የኢንስፔክሽ ኃላፊ የነበረው ተስፋዬ ደረጄ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አዘዘ።

ተከሳሹ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ተከሳሹ የሙስና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት በከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።

በዚህም በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ምርመራና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና ዳኛ ሆኖ ሲሰራ የማይገባውን ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የግል ተበዳይ የሆነው ሀ/ማርያም ገ/መስቀል የተባለ የግል ተበዳይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ሙስና ወንጀል ችሎት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ እየተከታተለ ባለበት ወቅት ማለትም በ2014 ዓ.ም ላይ ወደ ማረሚያ ቤት በመሄድ “እኔ በስራዬ ዳኛ ነኝ “የአንተን ጉዳይ እያዩ የሚገኙትን 3 ዳኞች መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አብሬያቸው ስለተማርኩኝ አውቃቸዋለሁኝ” በማለት ማግባባቱ በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም “ከዳኞቹ ጋር ተነጋግሬ በነፃ እንዲለቁህ አደርጋለሁ” በማለት የግል ተበዳዩን ካናገረ በኋላ በድጋሚ ወደ ተበዳይ በመሄድ “ዳኞቹን አናግሬ በብይን በነፃ እንድትለቀቅ 1 ሚሊየን 200 ሺህ ብር ጠይቀውኛል በማለት እንዲሁም “እኔ ተደራድሬ 600 ሺህ ብር አስደርጋለሁ” በማለት የማግባባት ስራ ሰርቷል በሚል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አመላክቷል።

በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ላይ ደግሞ “ዳኞቹ አሁን በቅድሚያ 400 ሺህ ብር ካልተከፈለን ምንም አናደርግም ብለዋል” በአስቸኳይ ብር አምጣ በማለት አሳሳች ነገር በመናገር እና የተበዳይን የተሳሳተ ዕምነት በመጠቀም አታሎ 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆነው የግል ተበዳይ ወንድም ከሆነው ግለሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም 400 ሺህ ብር የተቀበለ በመሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሹም ችሎት ቀርቦ ማንነቱን ካረጋገጠ በኋላ የቀረበበት ክስ ዝርዝር ደርሶት በንባብ እንዲሰማ ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ የተሰየመ ቢሆንም ተከሳሹ ግን የክስ መቃወሚያ እንደሌለው ለችሎቱ ገልጿል።

ተከሳሹ የተከሰሰበት ድንጋጌ የዋስትና መብት የሚያስከለክል መሆኑን ተከትሎ የዋስትና መብቱ ተገድቦ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ታዟል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ ለፍርድ ቤቱ የዕምነት ክህደት ቃል ሰጥቷል።

ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲሰሙለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም በተከሳሹ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለየካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version