አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ሁልጊዜም ፈጣን እንቅስቃሴ የሚስተዋልባት ከተማ ናት ሲሉ የተለያዩ ሀገራት ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ገለጹ፡፡
ለ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ በመዲናዋ ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ትዝብታቸውን አጋርተዋል፡፡
የናሚቢያ ሰን ጋዜጠኛ ቲዮማ ፋሂዱላ ፥ ከዋዜማው ጀምሮ በተደረገላት አቀባበል መደሰቷን፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች ቅንነት እና ተባባሪነትም እንደማረካት ተናግራለች።
በቆይታዋም በአፍሪካ ትልቁን ገበያ መርካቶን፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችን፣ የዕደ-ጥበብ መስሪያ ቦታዎችን ጨምሮ ባህላዊ ሬስቶራንቶችን እና የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስኅቦች ለመጎብኘት ማቀዷን ገልጻለች፡፡
ሴኔጋላዊው የአፍሪካ 24 ጋዜጠኛ አሊ መሐመድ በበኩሉ፥ አዲስ አበባ ሁልጊዜም ፈጣን እንቅስቃሴ የሚስተዋልባትና ደማቅ ከተማ መሆኗን በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች መመልከቱን አስታውሷል።
መዲናዋ የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያቀሉ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማከናወኗንም ጠቅሷል፡፡
የፒያሳ፣ መስቀል አደባባይ እና ቦሌ መንገድን ከዚህ ቀደም እንደሚያውቃቸው እና አሁን ላይ አስደናቂ ለውጥ ተደርጎባቸው መመልከቱ ተናግሯል።
ሌሎች በግልፅ የሚታዩ ለውጦች በትራንስፖርት እና በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ማየቱንም አንስቷል፡፡
አዲስ አበባ በርካታ ታሪክን የሚዘክሩ ቦታዎች አሏት፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለከተማዋ ሌላ መስኅብ ሆኗል ብሏል፡፡
አፍሪካውያን እንዲጎበኟቸው መክሮ ሊማሩባቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች በመታሰቢያው ውስጥ መኖራቸውን ገልጿል፡፡
እነዚህ ታሪኮች እንዲታወቁ እና ሌሎች እንዲማሩባቸው እየተሠራ ያለውን ሥራም አድንቋል፡፡
የአዲስ አበባ አዲስ ጽታዎች በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ ከተሞች መካከል አንዷ የሚያደርጋትን ፈጣን የልማት ጉዞ የጀመረች መሆኑን እንደሚያሳይም ነው ጋዜጠኞቹ የገለጹት፡፡
መዲናዋ ታሪካዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን አንስተውም፥ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥኑ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
በመዲናዋ በሚኖራቸው ቆይታም አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱን አካባቢዎች የመመልከት እንዲሁም ወዳጆቻቸው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የመጋበዝ ዕቅድ እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
በመራኦል ከድር

