Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 አምባሳደር ምስጋኑ ከደቡብ ኮሪያ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከደቡብ ኮሪያ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ቹንግ ቢዩንግ ዎን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው በመጪው ሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የኮሪያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዙሪያ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር፣ ንግድ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ በዚህ ወቅት እንደገለፁት÷ የኮሪያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ቀደም ሲል የነበረውን የኢትዮ-ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ታሪካዊው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ትብብር የበለጠ መጠናከር እንደሚገባው አጽንዕኖት ሰጥተዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ቹንግ ቢዩንግ ዎን በበኩላቸው÷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ልማት ለመለወጥ ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የሚካሄደው የኮሪያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ደቡብ ኮሪያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር እድሎችን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጉባኤው ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር የሚችሉና በሀገራቱ ተወካዮች በጉባኤው  የሚፈረሙ የትብብር ማዕቀፎችን እንድታዘጋጅ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version