አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳይበር ምሕዳር በተደጋጋሚ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች መካከል አንደኛው የማንነት ስርቆት ነው፡፡
በኮምፒዩተሮችና ሌሎች መሳሪያዎች ላይ የሚቀመጡ የግል መረጃዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚከተሉትን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ ማድረግ እጅጉን ይጠቅማል፡፡
እነዚህም፡-
• የተለያዩ የመረጃ ማስቀመጫ ዘዴዎችን “ባክአፕ” በመጠቀም መረጃዎትን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ያስቀምጡ፤
• ማናቸውንም የግል መረጃዎን እና የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች፣ የግል ማህደርዎን እና የይለፍ ቃልዎንም ለሌሎች ሰዎች አያጋሩ፡፡
• የግድ መገልገያ መሣሪያዎችንም ለሌሎች ሰዎች የሚያጋሩ ከሆነ አካውንትዎን ዘግተው መውጣትዎን ያረጋግጡ፡፡
• አካውንትዎን ሳይዘጉ የግል መሣሪያዎትን ለሌሎች ሰዎች ካዋሱ ካሉበት ርቀት ላይ ሆነው ዘግተው መውጣት ይችላሉ፤ ለዚህም የሚረዳዎትን ዕውቀት በማንበብ ማዳበር ይቸላሉ፡፡
• ሚስጥራዊ መረጃ የያዙ ኢ-ሜይሎችን በፍጹም በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ወደ ሌሎች ሰዎች አይላኩ፤
• ለሁሉም አካውንት ለየት ያሉና ከ12 በላይ ፊደላት ያሏቸው ረጅምና በቀላሉ ሊገመቱ የማይችሉ ጠንካራ የይለፍ ቃልን ይጠቀሙ፡፡ ለዚህም የይለፍ ቃል አስተዳደር ሊያግዝዎት ይችላል፤
• አካውንቶችን በመከታተል፣ ያልተለመደ እንቅስቃሴ በሚከሰት ጊዜ ማስጠንቀቂያዎችን ማግኘት እንዲችሉ የመስመር ላይ አገልግሎት ሰጪዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ፤
• ድረ ገጾች ላይ መረጃ በሚፈልጉበት ወቅት ሁልጊዜም የይለፍ ቃልዎን ከመጻፍዎ በፊት የድረ-ገጹን ዩ.አር.ኤል ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
• አጠራጣሪ ነገር ካጋጠመዎ በማፈላለጊያ መረቡ ላይ በመጻፍም ትክክለኛው አድራሻ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል፤
• ጠላፊዎች የሐሰት አካውንቶችን በመክፈትና ሰዎችን ጓደኛ በማድረግ ሊያጠምዱ ስለሚችሉ ይህንን በመገንዘብ ከማያውቁት ሰው ለሚቀርብልዎት የጓደኝነት ጥያቄ ምላሽ ትክክለኝነቱን ሳያጣሩ ፈጥነው ምላሽ አይስጡ፡፡