Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዳያስፖራው በልማትና ሰላም ግንባታ ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራው በልማትና በሰላም ግንባታ ላይ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ።

ጥሪው የቀረበው ‘ኮሚዩኒታችን ለጋራ አንድነታችን’ በሚል መሪ ሃሳብ በዱባይና ሰሜን ኤሚሬቶች ለ10ኛ ጊዜ በተከበረው ‘የኢትዮጵያ ቀን’ ላይ ነው።

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መድረኩን ሲከፍቱ ፥ ለማህበሩ መጠናከር ለሰሩ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መንግስትም ኢትዮጵያውያን ባህልና ታሪካቸውን እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም ለሀገራቸውም ሆነ ለሚኖሩበት ሀገር ልማት ሚናቸውን እንዲወጡ ዕድል በመስጠቱ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ልማት ያላቸው አስተዋዕኦ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል ሚኒስትር ዴዔታው፡፡

መንግስትም ከዳያስፖራው የሚገኙ ወረቶች እንዲያድጉና ዳያስፖራው በሚኖርባቸው ሀገራት መብትና ጥቅሙ እንዲከበር ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን መሰረት አድርጎ ከሀገራት ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ዜጎች በሚኖሩባቸው ሀገራት ሕግ አክባሪና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ እንዲሁም በሀገራቸው ልማትና ሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው በበኩላቸው፥ዳያስፖራው ለሀገራዊ ዕድገት የጀመራቸውን ተግባራት እንዲያሳድግና ሀሰተኛ መረጃዎች እንዲከላከል መጠየቃቸውን የአገልግሎቱ መረጀ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version