አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ የወጡ መመሪያዎችን በአግባቡ እንዲተገብር እና እንዳይዘናጋ የክልሉ ጤና ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ በወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ላይ በሰጠው መግለጫ÷ በአሁኑ ወቅት በለይቶ ማቆያ ውስጥ 228 ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል።
ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ምርመራ እየተደረገ መሆኑም ተነስቷል።
የክልሉ የጤና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ እንዳሉት÷ በክልሉ በቫይረሱ ከተያዙ 4 ሰዎች መካከል ሁለቱ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በሚቀጥሉት ቀናት ከለይቶ ማቆያው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ሃላፊዋ የገበያ ስፍራን ጨምሮ በሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ የማህበረሰቡ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ መደረግ ይገባዋልም ነው ያሉት።
በተለይም በክልሉ ተፈናቅለው ወደነበሩበት እየተመለሱ ያሉ ነዋሪዎች ከቫይረሱ ራሳቸውን እንዲጠበቁ ለማድረግ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ክልሉ ከሁለት ሃገራት ጋር ድንበር የሚዋሰን በመሆኑ ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የሚመጡ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባት ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።
በክልሉ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል ስድስቱ ድንበር የሚጋሩ ሲሆን አሁንም በተለይ በጉባ ወረዳ በኩል ድንበር ተሻግረው በተለያዩ መንገዶች የሚገቡ ስዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።
በወረዳዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ሲሉ ወይዘሮ ፍሬህይወት አንስተዋል።
በምስክር ስናፍቅ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

