Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የወላይታ ዞን ተወካዮችን መረጣ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህብረሰብ ተወካዮችን መረጣ ከየካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ አንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ እስከአሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በሰባት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳድሮች የተሳካ የተወካዮች መረጣ ማከናወኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በክልሉ12 ዞኖች ከዚህ በፊት ባሰለጣናቸው ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተወጣጡ ተባባሪ አካላት ታግዞ አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች ልየታን ያካሄዳል ብለዋል፡፡

ከየካቲት 19 እስከ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በወላይታ ዞን ከ23 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ የተወካዮች መረጣ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል፡፡

በተወካዮች መረጣ ላይም ሴቶች፣ ወጣቶች፣የንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

መረጣው አካታች፣ ግልጽ፣ አሳታፊና እና ተዓማኒ እንዲሆንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሒደቱ ከእያንዳንዱ የማሕበረሰብ ክፍል ሁለት ሁለት ተወካዮች ከአንድ አንድ ተጠባባቂ ጋር እንደሚመረጥ ጠቁመዋል፡፡

በማስተዋል አሰፋ

Exit mobile version