Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሆስፒታሉ ተቋርጦ የነበረውን የኩላሊት እጥበት ሕክምና ዳግም አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዳግማዊ ሚኒልክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተቋርጦ የነበረው የኩላሊት እጥበት ሕክምና ዳግም መጀመሩን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ÷ ሆስፒታሉ ቀደም ሲል የኩላሊት እጥበት ሕክምና አገልግሎት ከአብ ሜዲካል ሴንተር ጋር በትብብር ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአብ ሜዲካል ሴንተር ውሉን ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ማቋረጡን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ ተግባሩም በሕግ እንደሚጠየቅ ጠቁመው÷ ከተማ አስተዳደሩ የተቋረጠው ሕክምና በፍጥነት እንዲጀምር ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ሚድሮክ ግሩፕ ኢትዮጵያ ባደረገው የ40 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተጨማሪ 10 ማሽኖች በማስገባት የሕክምና አገልግሎቱ ዳግም መጀመሩን ሃላፊው አረጋግጠዋል፡፡

በሲሳይ ጌትነት

Exit mobile version