አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጉምሩክ ኮሚሽን ባደረገው ክትትል ከየካቲት 8 እስከ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ከ407 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ እንዳለው የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ፥ 263 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የገቢና 144 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የወጭ ፤ በድምሩ 407 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተይዘዋል፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይትና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል።
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዋሽ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት እና አዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ፥ በቅደም ተከተላቸውም 85፣ 81 እና 64 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራልና ክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውም ጠቁሞ፤ በህግ ማስከበሩ የተሳተፉትን አመስግኗል፡፡
ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 19 ተጠርጣሪዎችና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡

