Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ኖርዌይ የ75 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ኖርዌይ የ75 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል የተፈረመው ስምምነት ለሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

ስምምነቱ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ እንደአብነትም የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ መኖር፣ በደን መጨፍጨፍና መራቆት ምክንያት የሚመጣውን የካርበን ልቀት መቀነስ እና መሰል የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴዎችን አስመልክቶ ነው፡፡

ትብብሩ የኖርዌይን ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስና ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያን የደን ልማት አጀንዳ ወደ ፊት ለማራመድ አስተዋጽዖ እንዳለው ተነግሯል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ የኖርዌይ ህዝብና መንግስት ለኢትዮጵያ ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ይፋ ካደረገች በኋላ የኖርዌይ መንግስት ድጋፍ እንደቀጠለ መሆኑን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት መረጃ ያመላክታል።

የኖርዌይ የአየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አንድሪያስ ኤሪክሰን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላት ቁርጠኝነት በአርአያነት የሚጠቀስ በመሆኑ ሀገራቸው አጋርነቷንና ድጋፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

Exit mobile version