አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዛሬ ጀምሮ በቀጣዮቹ 10 ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የዝናብ መጠንና ስርጭቱ እየተስፋፋና እየተጠናከረ እንደሚሄድ ተመላከተ፡፡
በአጠቃላይ ጅማ፣ የኦሮሚያ ክልል ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብ አርሲና አርሲ ዞኖች፣ ባሌ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አዲስ አበባ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የዋግኽምራ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡
በጥቂት ስፍራዎቻቸውም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ መባሉን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጉጂ፣ የቦረና ዞን፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የአፋር ክልል ዞኖች፣ የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ እና የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ የሶማሌ ክልል ሲቲ፣ ፋፈን እና ዳዋ እንዲሁም ጥቂት የሊበን ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በጋምቤላ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ 38 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡