አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዛሬው ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን የአንድነት፣ የመተሳሰብና ትብብር ስነልቦና ሰንቆ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሒደት አርበኛ ሊሆን ይገባል ተባለ።
የአማራ ክልል እንኳን ለ128ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ ሲል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱም፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማሕተም፣ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና የነፃነት ተጋድሎ አርማ ነው ብሏል።
ድሉ በዓለም ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፤ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል መሆኑን ጠቅሶ፤ መላ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው ሀገራዊ ክብርንና ነጻነትን አስቀድመው በጋራ ዓላማቸው ላይ ከልብ የመግባት ውጤት ነበር ሲል ገልጿል።
ጀግኖች አባቶች በሀገር ፍቅር ስሜት ለክብርና ነጻነት ሲሉ የደም፣ የአካል ዋጋ ከፍለው ዳር ደንበሯ የተከበረ፤ ነጻነቷ የተረጋገጠ ሀገር ለትውልድ ማስረከባቸውን አስታውሷል።
የዛሬው ትውልድም ከአባቶቹ የወረሰውን የአንድነት፣ የመተሳሰብና ትብብር ስነልቦና ሰንቆ ሰላሟ የጸና በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሒደት አርበኛ ሊሆን ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።