Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የዓድዋ ድል በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለየዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች 128ኛውን ዓድዋ ድል በዓል አከበሩ፡፡

የዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል ‹‹ዓድዋ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት›› በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከብሯል፡፡

በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል፣ የዳያስፖራ አደረጃጀት አባላት፣ በጅዳና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

በተመሳሳይ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሀገሪቱ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት፣ የሐይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አክብሯል።

እንዲሁም በቴል አቪቭ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዓሉ የአድዋ ጀግኖችን በሚዘክሩ የተለያዩ መርሃግብሮች ተከብሯል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ÷የአድዋ ድል ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ መሆኑን ጠቅሰው ይህ አኩሪ ታሪክ ለሌሎች ድሎች መነሳሳትን የሚያወርስ ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የኤምባሲው ሰራተኞች ፣ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች እንግዶች መገኘታቸው ተመላክቷል።
በሌላ በኩል በኳታር ኤምባሲ አዘጋጅነት 128ኛው የአድዋ የድል በዓል ትውልደ ኢትዮጵያን በተገኙበት ተከብሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያዊያን የቀደምት አባቶቻችንን የተቀናጀ እና በአንድነት ላይ የተመሠረተ አኩሪ የድል ታሪክ በመጠቀም እና በወንድማማችነት መንፈስ በሀገር ልማት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ኋላ ቀርነትን ታሪክ በማድረግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በሀገር እዉን ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀዉ የአርበኝነት መገለጫ ነዉ ሲሉም ገልጸዋል።
Exit mobile version