አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛምቢያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጀኔራል ጂኦፍር ቾንጎ የተመራ የልዑካን ቡድን የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አጠቃላይ የትምህትና የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴን የዳሰሰ ጉብኝት አድርገዋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በጉበኝቱ ወቅት÷ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆኗ በወታደራዊ ልምድ ልውውጦች ጠቃሚ አቅም እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡
ጉብኝቱ ዛምቢያ ለምታደርገው ወታደራዊ ግንባታ የበለጠ አቅም እንደሚገኝበት በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው÷ ኮሌጁ የአፍሪካ ሀገራት እንደቤታቸው መጥተው የሚማሩበትና አቅም የሚያካብቱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሌጁ ወታደራዊ ትምህርቶችን ለመማርና የላቀ ዕውቀት መገብየት ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍት ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ አጠቃላይ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የመማር ማሥተማር ሂደት ምን እንደሚመስል ለዛምቢያ ልዑካን ቡድን ብርጋዲየር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡