Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

9 ተማሪዎች በሁዋዌ ክፍለ አህጉራዊ የአይሲቲ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል ቱኒዚያ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በ8ኛው የሁዋዌ ክፍለ አህጉራዊ የአይሲቲ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያን ወክለው ቱኒዚያ ገብተዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከጅማ፣ ከሐሮማያ እና አርባምንጭ ዩኒቨርስቲዎች የተገኙ ሲሆኑ ተማሪዎቹን ለማበረታታት ሶስት መምህራን አብረው መጓዛቸው ተገልጿል።

ዓመታዊው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተካሂዷል።

በውድድሩ የተመረጡ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቱኒዚያ በሚካሄደው 8ኛው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር 2023/24 ክፈለ አህጉራዊ የፍፃሜ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቱኒዚያ ይገኛሉ።

በውድድሩ ከኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ እና ሞሮኮ የተውጣጡ 90 ተማሪዎች እንደሚወዳደሩ ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የውድድሩ ተሳታፊዎች የሀገር አቀፍ ውድድር ተመርጠው ለክፍለ አህጉሩ የሁዋዌ አይሲቲ የማጠናቀቂያ ውድድር ያለፉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ውድድሩ በቱኒዚያ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

ሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ለዓለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተነደፈ የአይሲቲ ክህሎት ማሳደጊያና ማበልጸጊያ መድረክ ሲሆን የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚሰራ እንደሆነ ተነግሯል።

ባለፈው ዓመት በቻይና በተካሄደው 7ኛው የሁዋዌ ዓለምአቀፍ ውድድር ዘጠኝ ኢትዮጵያወያን ተማሪዎች ሦስተኛውን ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል።

Exit mobile version