አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ክልል መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ ከ10 ሺህ 500 በላይ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕስ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ በተከናወነው የህግ ማስከበር ስራ ክልሉ አዳጊ የሆነ የሰላምና ፀጥታ ውስጥ ይገኛል።
ክልሉ በተሟላ ሰላም ላይ መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው ህዝቡ በነጻነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ማከናወን ሲችል እንደሆነ የገለፁት ሰብሳቢው ከዚህ አንጻር አሁንም ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የፀጥታ አካላት በጋራ በመሆን ፅንፈኛ ቡድኑ ጥፋት ለመፈፀም ያደረገውን ሙከራ ማክሸፍ መቻሉን እና ሰራዊቱ የክልሉ መንግስት ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ መሆን እንደሚገባ አቋም ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በተደጋጋሚ በተደረገ የሰላም ጥሪና በህግ ማስከበር ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች ሰለሰላም ዋጋ አስፈላጊነት በተሰጣቸው የተሃድሶ ስልጠና እራሳቸውም የሰላም ዘብ ለለመሆን ሃላፊነት እየወሰዱ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
እስከ አሁን በተደረገ ጥረት ከአስር ሺህ 500 በላይ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
መንግስት ሁሉንም ችግሮች በሰላምና በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ÷ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት ወራት በታጣቂ ቡድን በርካታ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ በደረሰ ውድመት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡንም ገልጸዋል።
መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባውን ማዳበሪያ ሳይቀር ቡድኑ እየዘረፈ ለግል ጥቅሙ እያዋለ መሆኑን አውስተው፤ ይህንን ከህዝብ ጥቅም በተቃራኒ የሆነ ተግባር የሚፈጽመውን ህዝቡ አምርሮ ሊታገለው ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የተገኘውን ሰላም በማፅናት ህግ የማስክበር ስራውን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡