አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መምህራን፣ የትምህርት አመራርና የትምህርት ባለሙያዎች ከነገ ጀምሮ በማህበር መደራጀት ይጀምራሉ ተባለ።
መምህራንን በሕብረት ሥራ ማህበራት በማደራጀት የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የተጀመረው ስራው የመምህራንን የቤት ችግር መፍታት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱንም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ መምህራንን በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት መኖሪያ ቤት ለመገንባት ስራ መጀመሩን አስታውሰዋል።
ይህ የተጀመረው ስራ የመምህራንን የቤት ችግር መፍታት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን መረጃዎችና ሰነዶች የተጣሩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ከህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ፈቃድ በማግኘት ከነገ ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መምህራን፣ የትምህርት አመራሩና የትምህርት ባለሙያው በማህበር መደራጀት የሚጀምሩ ይሆናል ብለዋል፡፡
በዚህም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ30 ሺህ በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሮች እንደሚደራጁ ጠቁመዋል።
የዚህ እድል ተጠቃሚ የሆኑ መምህራን ከተደራጁ በኋላ 30 በመቶ መቆጠብ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም 70 በመቶው ከፋይናንስ ተቋማት በብድር አቅርቦት እንደሚመቻችም ተመላክቷል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ