አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጀርመን በሰላምና ልማት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች ይበልጥ ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የጀርመን የፓርላማ አባላት ልዑካን ጋር ተወያይቷል።
የውይይቱ ዋነኛ ጉዳይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) ፥ ኢትዮጵያና ጀርመን የቆየ ታሪካዊ፣ የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር መስኮች፣ በሰላምና በጂኦ-ፖለቲካ ዘርፎች ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በማዕድን፣ በማምረቻውና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሳተፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያን አጠቃላይ የልማትና የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ እንዲሁም የባህር በር ለማግኘት እያከናወነች ያለውን ጥረት በተመለከተም አብራርተዋል ዲማ (ዶ/ር) ።
ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነትም ይህንን ጥያቄ በመመለስ፣ በጋራ በመልማት፣ የአካባቢ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የተፈጥሮ ሃብትን በጋራ መጠቀምንና በኃይል ልማት ትስስር ለመፍጠር የተገነባው የሕዳሴ ግድብም ግንባታው በመገባደድ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጀርመን ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ስቴፋን ኪዩተር እንዳሉት፥ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላት።
የጀርመን ፓርላማ አባልና የአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ እና የምጣኔ ኃብትና ልማት ትብብር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲፕል ዲሚተር ፍሪዶፍ ፥ በዓለም እንዲሁም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ ተቀራርባ የምትሰራ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።
የጀርመንና የኢትዮጵያ ፓርላማ ተወካዮች የሁለቱን ሀገራት በምጣኔ ኃብት፣ በፖለቲካ፣ በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት፣ በሰላምና በሌሎችም የትብብር መስኮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ በውይይታቸው ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
#Ethiopia #German
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!