አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ወንድም ሕዝቦች መዳረሻ ናት ሲሉ የዛምቢያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ጂኦፍር ቾንጎ ተናገሩ፡፡
በምክትል ኢታማዦር ሹሙ የተመራ ከፍተኛ የዛምቢያ ወታደራዊ አመራሮች ልዑክ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ እያከናወናቸው ያሉ የትምህርት፣ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡
ምክትል ኢታማዦር ሹሙ በወቅቱ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕዝቦች መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰዋል።
አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን ልኅቀት በትብብር በመሥራት አኅጉራዊ፣ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ለውጦችን በስኬታማነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራትም በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች አተኩረው በመሥራት የዘመኑን ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ልኅቀት በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እያረጋገጡ ውጤቱን በፍጥነት መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በጠንካራ ወታደራዊ አደረጃጀት የምትታወቀው ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏን ለማዘመን የምታደርገው የትምህርት፣ የጥናትና የምርምር ሂደት እንደሚደነቅ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞችም በጋራ እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ለልዑኩ በሰጡት ገለጻ÷ ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቷ የምትጠይቀውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተቃኘ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ለማረጋገጥ ከአጭር የትምህርት ፕሮግራም እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በተለያዩ የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ አተኩሮ በልኅቀት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሚሰጠው ውጤታማ ትምህርትና ስልጠና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተመራጭ በመሆኑ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ወታደራዊ መኮንኖችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡