አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል ድርጊት ከ39 የአፍሪካ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጋር ሲነፃፀር ሦስትኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ጥናት አመላከተ፡፡
መቀመጫውን ጋና አክራ ያደረገው አፍሮ ባሮሜትር የተባለ ተቋም በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በ39 የአፍሪካ ሀገራት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት የኢትዮጵያ ፖሊስ ከሞሮኮና ታንዛኒያ ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ፖሊስ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ አወሳሰድን በተመለከተም÷ ከሲሼልስ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪታኒያ ቀጥሎ አራተኛ ደረጃ መያዙን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ተቋሙ ፖሊስ የፈጠረውን የሕዝብ አመኔታ አስመልክቶ ባደረገው ጥናት የኢትዮጵያ ፖሊስ ከ39 የአፍሪካ ሀገራት መካከል 12ኛ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በፖሊሳዊ ሙያ መሠረት በመሥራት የዜጎችን መብት አክብሮ አገልግሎት በመስጠት ረገድም ከ39 የአፍሪካ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት መካከል 13ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
አፍሮ ባሮሜትር ከ2021 እስከ 2023 ባካሄደው ጥናት በ39 የአፍሪካ ሀገራት ፖሊስ ተቋማት ስለ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ ስለ ሙስና፣ የፖሊስ አባላት በወንጀል ድርጊቶች ስላላቸው ተሳትፎ፣ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ አወሳሰድንና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ባካሄደው ጥናትና የሕዝብ አስተያየት ትንተና መሠረት ነው ደረጃውን ያስቀመጠው።