Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ላይ ያተኮረ ውይይት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅግጅጋ ዩኒቨርሰቲ እና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ላይ ያተኮረ ውይይት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

“የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና የመልካ ፖለቲካ አንድምታ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

ውይይቱ የኢትዮጵያ ቀጣይ ዕድል ላይ የምንወያይበት ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በሽር አብዱላሂ (ዶ/ር) ፥ መድረኩ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን በጋራ የመልማት ጥያቄ በተመለከተ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስችልም አንስተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለባህር በር ቅርበት ያላት ሀገር ብትሆንም በታሪክ አጋጣሚ የባህር በርን የመጠቀም ፍላጎቷ በሌሎች ሀገር ፈቃድ ላይ ጥገኛ ሁኗል ብለዋል።

በለውጡ ማግስት እነዚህንና መሰል ስብራቶች ለመጠገን ጥረቶች ሲደረጉ እንደቆዩ አስታውሰው ፥ በዲፕሎማሲያዊና በጋራ መልማት መርህ የባህር በርን የማልማት ጥያቄ ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተር ጄኔራሉ እንዳሉት ፥ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ታሪካዊ ስብራቶቻችንን ለመጠገን፣ ላስመዘገብናቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ዘላቂነት እንዲሁም ከመልክዓምድራዊ እስራቶች መውጫ መንገድ ነው።

በውይይት መድረኩም ፥ “የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና የመልካ-ፖለቲካ” እንዲሁም “የባሕር በር ማልማት የውጪ ፖሊሲ ግብ” የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

በመራኦል ከድር

Exit mobile version