Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር አቀፍ የፖሊስ ገለልተኛ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 ዓ.ም የተቋቋመው ሀገር አቀፍ የፖሊስ ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በስብሰባው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ የገለልተኛ ምክር ቤቱን ስራ የሚመሩ ሰባት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ክልሎች እና ኢትዮጵያን በሚወክል መልኩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በሥራ አስፈጻሚነት ሲሳተፉ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በቀላሉ ህብረተሰቡ ዘንድ ለመድረስ ዩኒቨርሲቲዎች ምቹ ስለሆኑ በምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ በማካተት ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችንም በመያዝ የፖሊስ ስራና ህብረተሰቡን በተሻለ ደረጃ ማገናኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ዘመናዊ በሆነ መልኩ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ለማሳደግ ትልቅ እድል የሚፈጥረውን የዜጎች ትስስር የሞባይል መተግበርያም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአማካሪ ምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በፌደራል ፖሊስ ሪፎርም የለሙ የቴክኖሎጂ አቅሞችን እንደጎበኙም ተገልጿል፡፡

Exit mobile version