Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከኢንፔሪያልና ሪቬራ ሆቴል ግዢ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከኢንፔሪያል እና ሪቬራ ሆቴል ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው።

የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ላይ በ2011 ዓ.ም ከህግ ውጪ በተፈጸመ ኢንፔሪያል እና ሪቬራ በተባሉ ሁለት ሆቴሎች ግዢ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል በማለት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቧል።

ይህንን ተከትሎ ተከሳሹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መነሻ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ የሰነድና የሰው ምስክሮችን በችሎት አቅርቦ አሰምቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ሜጀር ጀነራል ክንፈ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ በተገቢው መከላከል አለመቻላቸውን ዛሬ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፤ በወንጀል ህግ አንቀጽ 407 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

በተላለፈው የጥፋተኝነት ፍርድ በአንደኛው የሆቴል ግዢ በሙሉ ድምጽ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፣ በሌላኛው የሆቴል ግዢ ክስ ደግሞ በአብላጫ ድምጽ በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከዚህ በፊት ከ111 የራዳር ግዢ ጋር ተያይዞ በ3 ዓመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በ4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ውሳኔ መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በአሁን ወቅትም በሜጀር ጀነራል ክንፈ ላይ የመርከብ ግዢን ጨምሮ ሶስት ቀሪ የሙስና የክስ መዝገቦች በፍርድ ቤት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version