Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ህገወጥ ተግባር በፈጸሙ 205 ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ 205 ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

የደንበኞችን ጥያቄ ለመመለስ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የፓስፖርት ቡክሌት ሕትመት መከናወኑንም ነው አገልግሎቱ የገለጸው።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት÷ የአገልግሎቱን የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በሥድስት ወራት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የፓስፖርት ቡክሌት ታትሞ ታትሞ ከ640 ሺህ በላይ የሚሆነው ለደንበኞች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ይሄም የፖስፖርት ህትመት ክፍሉ በትጋት በመስራት ያመጣው ውጤት መሆኑን ጠቅሰው÷ ከመጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በኋላ ዜጎች በተሰጣቸው የቀን ቀጠሮ መሰረት ፓስፖርታቸውን መረከብ ይችላሉ ብለዋል።

ባለፋት ስድስት ወራት 205 ከውጭ አገር ደላሎች ጋር ተመሳጥረው በህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ከስራ እስከማባረር የደረሰ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ገልጸዋል።

ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸውና ባልተፈቀደላቸው ስራ ላይ የተሰማሩ ከ10 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ምርመራ በማድረግ እንደ ጥፋት መጠናቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓልም መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ሰነድ አሟልተው እንዲመዘገቡ መደረጉም ተገልጿል፡፡

 

Exit mobile version