አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት ዘርፍ የሚታየውን ስብራት ለመጠገንና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በቁርጠኝነት መስራትን ይጠይቃል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር (ዶ/ር፣ ኢ/ር) ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ”የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ቁርጠኝነት ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል” በሚል መሪ ሀሳብ ከትምህርት ቤት አመራሮችና መምህራን ጋር የተማሪዎች ውጤትና ተሳትፎ ማሻሻል ላይ ያተኮረ ክልላዊ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) እንደገለጹት÷ በትምህርት ዘርፍ የሚታየውን ስብራት ለመጠገን፣ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በቁርጠኝነት መስራትን ይጠይቃል።
በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ተሳትፎ ማሳደግና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶችን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የተመዘገበውን ዝቅተኛ የተማሪዎች ውጤት በቀጣይ ለማረም በትብብር መስራት ይጠበቅብናልም ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው÷ የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት ከመምህራንና ከትምህርት ቤት አመራሮች ጋር መምከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

