Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሺዎች የሚቆጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት ለሕዝብ ክፍት የተደረገው የዓድዋ ድል መታሰቢያን በሺዎች የሚቆጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከዛሬ ጀምሮ ለሕዝብ እይታ ክፍት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች፣ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ዳያስፖራዎች፣ የውጭ ሀገራት ዜጎችና ከተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ ሰዎች ጎብኝተዋል ተብሏል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ፥ በአፈታሪክ ብቻ ከልጅ ልጅ ሲሻገር የነበረውን የዓድዋ ድል ምናብ ከሳች በሆነ መልኩ ሳይሸራረፍ ለትውልድ የሚያሻግር ቅርስ ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በድሉ ኢትዮጵያውያን ጽናትን፣ አንድነትንና ህብረትን አሳይተውናል ያሉት ጎብኚዎቹ ፥ ይህ ጽናትና አንድነት ለቀጣዩ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድም መታሰቢያው ማስተማሪያ ሆኖ መቆሙን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያውያን ብሎም የጥቁር ሕዝቦች ድል ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል ታሪክ ገላጭ በሆነ መልኩ በጥራት በመሰነዱ ሀገሪቱ በመስዋዕትንት የተገኘች ሀገር መሆኗን በማመላከት በትውልዱ ላይ የሀገር ፍቅር ስሜት ማስረፅ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀጣዩ ትወልድ ዳር ድንበሩን ለማስጠበቅ የተቆርቋሪነት ስሜት እንዲኖረው እንደሚያስችል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ውባየሁ ማሞ (ኢ/ር) ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ ተማሪዎች በበኩላቸው ፥ የኢትዮጵያውን ድል ብሎም የአፍሪካዊያን ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል ታሪክ በቃል ከተማሩት በላይ በመታሰቢያው የዘመኑን ትውስታ በሚጭር መልኩ አግኝተነዋል ነው ያሉት፡፡

ጎብኚ የዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህራን እንዳሉት፥ የድል መታሰቢያው የታሪክን እውነትነት ዛሬ ላይ እንደሆነ አድርጎ ያሳያል፡፡

በተለይም ለታሪክ ተማሪዎች፣ ለምሁራን፣ለመጻህፍት፣ ለውጭ ሀገር ጎብኚዎችና ለመሰል አካላት ሁሉ ምስል ከሳች በሆነ መልኩ እንደ ቤተ ሙከራ ሊያገለግል የሚችል ውድ ቅርስ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡም ታሪካዊ የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲጎበኝ ጥሪ ተደርጓል፡፡

Exit mobile version