Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለበርካታ ዓመታት የቆየውን የኢትዮጵያና የስዊዘርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት ከስዊዘርላንድ አቻቸው ኢግናዚዮ ካሲስ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ÷ ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ ግንኙነታቸውን በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ÷ በርካታ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት መሰማራታቸውን ጠቁመው ይህንን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ከዚህ ቀደም የተደረሱ የትብብር ሥምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግም መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።

በሌላ በኩል በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት፣ በሽግግር ፍትህና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአፈፃጸም ሂደት ላይ አጽንዖት ሰጥተው መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡

ኢግናዚዮ ካሲስ በበኩላቸው÷ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ለማስቀጠል መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ወሳኝ ሚና የምትጫወት ሀገር መሆኗን መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፍልሰት ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።

Exit mobile version