አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው÷ የመሬት ይዞታ እንዲለቀቅ የተፈለገው የመሰረተ ልማት ስራዎች በሚከናወኑበት ጊዜ ንብረት ለመገመት፣ የመክፈልና የማስነሳት ስራ ሙሉ በሙሉ ለክልሎችና ለከተማ አሥተዳደር አካላት መስጠት እና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ አሠራር ለመዘርጋት ነው ተብሏል፡፡
ማሻሻያውን ማድረግም ፕሮጀክቶች አዋጭ በሆነ መንገድ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና በተሰጣቸው ወጪ ለመፈጽም ዕድል እንደሚሰጥ የምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ የነበሩ የካሣ ጥያቄዎች እንዲፈቱ የሚያስችል አሰራር አዋጁ ላይ እንዲቀመጥ በመግለጽ የተጠያቂነት ችግር እና እንግልት እንዳይኖርም በሚሻሻለው አንቀጽ ላይ መመላከት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ካሳ በመክፈል በኩልም የፌደራል መንግስት እና የክልሎች መንግስታት የሚተባበሩበት እና በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ እንዲካተትም አስገንዝበዋል፡፡
በምክር ቤት አባላት የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምሮ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 12/2016 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች እንዲሁም በተባባሪነት ለሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል፡፡
በየሻምበል ምኅረት

