Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባለቤቱ ሳያውቅ ባለ 3 መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤትን በሀሰተኛ ሰነድ የሸጡ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለቤቱ ሳያውቅ ባለ 3 መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤትን በሀሰተኛ ሰነድ በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሸጠዋል የተባሉ ግለሰቦች በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጠ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል በጳውሎስ ገለጠው፣ ዳዊት ግርማ እና ፋሲል እሸቱ ላይ በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በተለይም በአንደኛ እና ሁለተኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ጳውሎስ ገለጠው ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 ሀ፣ 2 እና 3 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌን በመተላለፍ እንዲሁም የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 አንቀጽ 66/1 በመተላለፍ፤ በተመሳሳይ ስም በተዘጋጀ ሀሰተኛ መታወቂያ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም በብድር ውል በኮዬ ፈጬ ሳይት በሚገኝ ባለ 3 መኝታ ቤትን የእኔ ነው በማለት የቤቱ ህጋዊ ባለቤት ሳይሰማና ሳያውቅ ቤቱን ሸጧል ተብሎ የቀረበ ነው።

3ኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በዚህም 1ኛ ተከሳሽ የእኔ ቤት ነው ብሎ በብድር ውል በህገ ወጥ መንገድ የቤቱ ህጋዊ ባለቤት ሳያውቅ በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በሸጠበት ወቅት 2ኛ ተከሳሽ ለቤቱ ገዢ 1ኛ ተከሳሽ የቤቱ ባለቤት ነው ብሎ በሀሰት አሻሽጧል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።

በሌላኛው ክስ ደግሞ በሁሉም ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ቤቱን ከተሸጠ በኋላ ገንዘቡን በተለያየ መጠን በባንክ ሂሳባቸው በማዘዋወር ለግል ጥቅማቸው አውለውታል በማለት ነበር ዐቃቤ ሕግ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ሙስና ወንጀል ክስ ያቀረበው።

ተከሳሾቹ ችሎት ከቀረቡና ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ማስረጃ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱ የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሰረት ተከሳሾቹ በተገቢው መንገድ መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ ጳውሎስ ገለጠው ያቀረበውን 6 የቅጣት ማቅለያን በመያዝ በዕርከን 27 መሰረት በ8 ዓመት ከ5 ወራት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

2ኛ ተከሳሽ ዳዊት ግርማን ደግሞ በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ፋሲካ እሸቱ ደግሞ በ5 ዓመት ጽኑ እስራት በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version