Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቲቢን ለመግታት የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2030 ቲቢን ለመግታት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት በቀጣይ ሰባት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

18ኛው ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጉባዔው ላይ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመግታት በፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት አማካኝነት ባለፉት 20 ዓመታት ጥናትና ምርምሮችን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ተግባራት አከናውናለች፡፡

ይህ ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ አማካኝነት የቲቢ በሽታን ለመቀነስ በተከናወነ ተግባር ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2020 ስርጭቱን በ31 ነጥብ 3 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የሞት ምጣኔውን ደግሞ 34 ነጥብ 6 በመቶ መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በፈረንጆቹ 2030 ቲቢን ለመግታት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረትም በቀጣይ ሰባት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ጠቁመው÷ ለውጤታማነቱ ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

Exit mobile version