አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያመነጫቸው መረጃዎች ለፀጥታ አካላት ስምሪት አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር የሀገሪቱ ፀጥታ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው ተገለጸ።
የአገልግሎቱ የ2016 በጀት አመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጻም የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመሩት መድረክ ተገምግሟል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ የሀገርን ደኅንነት የሚያስጠብቁ መረጃዎችን በማመንጨት እና ለፈፃሚ አካላት በማቅረብ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉትን የፀጥታ ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ የመረጃና የኦፕሬሽን ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከት መቻሉን ገልጿል።
የአፍሪካ ሕብረትን ዓመታዊ ጉባኤን ጨምሮ ሌሎችም ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁም ተቋማዊ ሚናውን በላቀ ስኬት መወጣቱም ተመላክቷል።
የአገልግሎቱ የተልዕኮ ሥራዎች ውጤታማነት በሀገር ደኅንነት ከባቢ ላይ ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ አንጻር መለካት እንዳለባቸው በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በስድስት ወራት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸው መገምገሙን ጠቁሟል።
በዚህም ለፀጥታ አካላት አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ በአንጻራዊነት እንዲሻሻል አገልግሎቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተነግሯል።
የአገልግሎቱ መረጃ የመሰብሰብ እና የመፈጸም አቅም በመጨመሩ ምክንያት እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት ባሕሉ በመጠናከሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይታዩ የነበሩ የፀጥታ ችግሮች እየተሻሻሉ መምጣታቸው ተጠቁሟል፡፡
ዕቅዱ ሀገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ሁኔታ አንጻር እንዲሁም በቀጣናው ያለው የደኅንነትና የፖለቲካ ሁኔታ ውስብስብ እየሆነና እየተባባሰ በሚገኝበት አውድ የተፈጸመ ከመሆኑ አንፃር ስኬታማ ነበር ማለት እንደሚቻል ተመላክቷል።
የአገልግሎቱን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሎጂስቲክስ እና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ረገድም ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን መረጃው አስታውቋል።
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አጋርና አቻ ተቋማት ከአገልግሎቱ ጋር በትብብር ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸው የተቋሙ የመፈጸም አቅምና የተጽዕኖ አድማስ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል ያለው መረጃው፤ በቀጣይም ይህንን ለማጎልበት ስትራቴጂያዊ በሆኑ ተልዕኮዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
አገልግሎቱ መረጃዎችን የማመንጨትና ትንበያዎችን የማስቀመጥ አቅሙ በማደጉ በቀጣናው ከሚታዩት ፈጣንና ተለዋዋጭ የደኅንነት ሁኔታዎች አንፃር ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን የሚያስጠብቁ ስምሪቶች ከማከናወን ባሻገር ከተለያዩ ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ሂደቱ እየጨመረ መምጣቱ ተመልክቷል።
በዚህም ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያና የሰዎች ዝውውርን እንዲሁም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ተችሏል ብሏል፡፡
በቀጣይም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈፀሙ የውንብድና ወንጀሎችን ተከታትሎ መረጃ በማጥራትና በማጠናቀር ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችሉ ስምሪቶች እንደሚከናወኑ ተመልክቷል።
በሀገር ውስጥ ያለውን የፀጥታ እና ደኅንነት ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግም ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን የሚያመጡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ማምረት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የኢኮኖሚ አሻጥር በተለይ የሀብት ሽሽት ላይ እንዲሁም ከኤርፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከተቋሙ የተልዕኮ ማዕቀፍ አንጻር አስተማማኝ የደኅንነት ሁኔታ እንዲሰፍንና የተገልጋዮች ቅሬታ እንዳይፈጠር የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩም የተቋሙ መረጃ አመልክቷል።

