አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን በዓለም አቀፋዊነትና አመራርን ለማጠናከር የሚውል የ1 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ደጋፍ መገኘቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የ1 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ድጋፉ የተገኘው ኢትዮጵያ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ የዩኒቨርሲቲ አጋርነት በኩል በሚመራው የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩልበ መመረጧ መሆን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ገልጿል።
ድጋፉ እውቀትን ማካፈልና መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋፋት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ነው ኤምባሲው የገለፀው ፡፡
በድጋፉም ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሁለት ፕሮጀክቶች መመረጣቸውም ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያው ፕሮጀክት በዓለማቀፋዊነት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን የአቅም ግንባታ እና ጥራት ማሻሻያ ላይ የሚሰራ ሲሆን በአሜሪካው ኢንዲያና ዩኒቨርስቲ የሚመራ ሆኖ የቢዝነስ ስራ ፈጠራ አጋርነት እና የአመራር ሽግግር የሚል አርዕስት ተሰጥቶታል፡
ይህ ፕሮጀክት የሁለት ዓመት ሲሆን በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ያለውን ሃብ የማጠናከር እና ኢንዲያና ዩኒቨርስቲ እና አይቬ ኮሙኒቲ ኮሌጅ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር አዲስ ሃብ ዩኒቨርስቲው ላይ የሚከፍቱበት ይሆናል ተብሏል፡፡
ሁለተኛው ፕሮጀክት የ3 ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን በቴክሳስ ቴክ ዩኒቨርስቲ እንደሚመራ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው በትምህርት አመራር ማኔጅመንትና አስተዳደር ላይ ነው፡፡ በዚህም ቴክሳስ ቴክ ዩኒቨርስቲ፣ ኦሃዩ ስቴት ዩኒቨርስቲ፣ኦክላሆማ ስቴት ዩኒቨርስቲ እና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ግሎባል ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለከፍተኛ ትምህርት አመራሮች የሚሰጡበት እንደሚሆን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ

