Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመጀመሪያው ዙር ከ74 ሺህ በላይ የ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መጥተዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪን በመቀበል በመጀመሪያ ዙር ብቻ ከ74 ሺህ በላይ በውጭ የሚኖሩ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸውን የኢትዮጰያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታሕሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጰያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ነብዩ ሰለሞን አንደገለጹት÷ ጥሪው በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተላለፈ መሆኑን አንስተዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ”ከብዝሃ ባህልና ማንነት ጋር መገናኘት” በሚል ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም መከናወኑን ጠቁመው÷ ይህም የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጥሪውን በመቀበልም በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ74 ሺህ በላይ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተዋል ነው ያሉት።

ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በሚመለከት በተገቢው መልኩ የማስተዋወቅና የማስጎብኘት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

ጥሪውን ተቀብለው የመጡት እንግዶችም ሀገራቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ በልማት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ቃል በመግባት ያረጋገጡበት በመሆኑ ቆይታቸው ስኬታማ እንደነበር ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ምዕራፍ ጥሪ በይፋ መጀመሩን ጠቁመው ፥ ጥሪው እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ተናግረዋል፡፡

ጥሪው ”ታሪካዊ መሰረቶን ይወቁ” በሚል እየተከናወነ ሲሆን ÷ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ታሪክና ቅርስ ጋር የሚተዋወቁበት እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡

የዓድዋ ታሪክን መነሻ በማድረግ ለጉብኝት ክፍት የሆነው የዓድዋ ሙዝየምን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን የሚጎበኙበት እድሎች ተመቻችተዋል ነው ያሉት።

Exit mobile version