Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመጪዎቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ ይጠናከራል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪዎቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ እየተጠናከረና እየተስፋፋ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አመላከተ፡፡

በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት ምስራቅ ሸዋ፣ አዲስ አበባ፣ ምስራቅ አማራ፣ ሀረር፣ ድሬዳዋ እና አይሻ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብሏል ኢንስቲትዩቱ፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፥ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የሱማሌ ክልል ዞኖች ተመሳሳይ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቀሙሟል፡፡

በተጨማሪም ከአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ፣ የመካከለኛው እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የዋግኸምራ ዞኖች፣ ከጋምቤላ ክልል የአኛዋክ እና የመዥንግ ዞኖች፣ ከቤንሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማኦኮሞ ልዩ ወረዳ፣ ከትግራይ ክልል የመካከለኛው ትግራይ ዞን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version