Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ከ670 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች መረጃን ዲጂታል ማድረግ ተችሏል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ 670 ሺህ 568 የመሬት ይዞታዎች መረጃን ዲጂታል ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችንና ሌብነትን ለመከላከል ላለፉት 6 ወራት የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

የመሬት መረጃዎችን ዲጂታል የማድረግና በአንድ ቋት የመጫን ስራዎችም ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም 670 ሺህ 568 መረጃዎች አዲስ ኮድ ተሰጥቷቸው እንደአዲስ መደራጀታቸውንና 27 የተቋሙ አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለምቶ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም አገልግሎቶችን ከተለያዩ መረጃዎችና የዲጂታል ክፍያ ዘዴዎች ጋር ማስተሳሰር እንደተቻለ አቶ ሲሳይ ገልፀዋል።

ቢሮው አገልግሎቶችን ለማዘመንና ፍትሃዊ ለማድረግ የሰራው ሪፎርም ወደ ስራ መግባቱም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

በአፈወርቅ እያዩና ሜሮን ሙሉጌታ

Exit mobile version