Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮ ቴሌኮም ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተፈራረመ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮምና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የስማርት የመማሪያ ክፍሎችን በክልሉ በተመረጡ 8 አዳሪ ትምህርት ቤቶችና 33 ልዩ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን አሟልቶ ለማቅረብ የሚያችል መሆኑ ተገልጿል።

ይህም ስራ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና የትምህርት አሰጣጥ ስርአቱን በማዘመን ተማሪዎች ጥራት ያለውና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ፣ ፍትሃዊ የሆነ የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖበታል፡፡

እንዲሁም የዲጂታል ትምህርት ትራንስፎርሜሽን እንዲተገብሩና የትምህርት ግብዓቶች እጥረትን ለመቅረፍ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በክልሉ ከ11 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች እና 35 ሺህ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

የስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ተግባራዊ ማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ በሚደረገው ሂደት ውስጥ የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በማህሌት ተ/ብርሃን

Exit mobile version