Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በወርቅ ምርት ላይ ያለውን ችግር ለይተን እየሰራን ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅ ምርት ላይ ያለውን ችግር ለይተን እየሰራን ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በርካታ ማህበራትን አደራጅተን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ አድርገናል ብለዋል፡፡

ይህም ባለፉት ዓመታት የተሻለ የወርቅ ምርት እንዲገኝ በማድረጉ ወደ ባንክ የሚገባው ምርት ጨምሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጥቁር ገበያ ካለው ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ወርቅ እየተመረተ ወደ ባንክ የማይገባበት ሁኔታ እንዳለ ተገምግሞ ችግሩን በአግባቡ ለይተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራበት እንደሆነም ነው ያመላከቱት፡፡

ከችግሩ ውስጥም ባንክ የሚቀበልበት እና ጥቁር ገበያ ላይ ያለው ዋጋ በግራም በጣም ልዩነት መኖር፣ የባንኮች ተደራሽነት ችግሮችና የኮንትሮባንድ መስፋፋት እንደሚጠቀስ ገልፀዋል፡፡

በአጠቃላይ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለፉት ጊዜያት እቅድ አዘጋጅተናል፤ በየደረጃው ግብረ ሃይል ለማቋቋም ጥረት አድርገናል ብለዋል።

ዘርፉ በማህበራት ብቻ ከሚወሰን ካምፓኒዎችን ማስገባት እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ የጠቆሙት፡፡

ይህ ከሆነ የሚፈለገውን ያህል የወርቅ ምርት ወደ ባንክ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚፈጠር እና በአጠቃላይ እየተወሰዱ ባሉ ርምጃዎች ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version