አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመንግስት ተሿሚዎችና የህዝበ ተመራጮችን ሃብት መዝግቦ ያለ ገደብ ለህዝብ ክፍት የሚሆንበትን አሰራር እየዘረጋ መሆኑን የፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ፥ የዘመናዊ ሃብት ምዝገባ መረጃ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጉን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ስርዓቱ ከዚህ ቀደም በማኑዋል የነበረውን አሰራር ወደ ዲጂታል የሚቀይር መሆኑም ተነግሯል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም እስከ ሁለት ወር ይፈጅ የነበረን የምዝገባ ሂደት ተመዝጋቢው ባለበት ሆኖ በሁለት ደቂቃ ማከናወን የሚያሰችለው መሆኑ ተገልጿል።
የኮሚሽኑ የሃበት ማሳወቅ እና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይ እንደተናገሩት፥ የተዘረጋው ስርአት ኮሚሽኑ የተመዘገበውን መረጃ ለሀብረተሰብ ለማሳወቅና ተደራሽ ለማድረግ ከጊዜና ከወጪ እንዲሁም ከርቀት አንጻር የነበረበትን በርካታ ችግር ይፈታል።
እስካሁን ባለው ከሱማሌ እና አፋር ክልል ውጪ 500 ሺህ የሚደርሱ ተሿሚ፣ ተመራጭና የሚመለከታቸው አካላት ሃብታቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን ወደ መረጃቸው አዲሱ ስርዓት እንዲገባ እየተደረገ ነው መሆኑንም በመግለጫው ተነስቷል።
አዲሱ አሰራር የምዝገባ ሂደትን ከማቅለል በተጨማሪ የመንግስት ተሿሚዎችና የህዝበ ተመራጮችን ሃብት ለህዝብ ክፍት የሚያደርግ መሆኑም ታውቋል።
በሀይለኢየሱስ ስዩም
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

