አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊቼ ጨምበላላን የእርቅና የይቅርታ እሴቶች ችግሮቻችንን መፍቺያ አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የፍቼ ጨምበላላ የዋዜማው በዓል በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ላይ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን የሲዳማ የባህል ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚየም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የብሔሩ ተወላጆች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
አቶ ደስታ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፍቼ ጨምበላላ ጠቃሚ እሴቶችን የያዘ በመሆኑ ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልዘመነበት ወቅት የሲዳማ አባቶች ተፈጥሮን አንብበው ጊዜ ያሰሉ ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ስርአቱም የቀን፣ የሰዓታትና የዓመታትን ቀመር የያዘ ነው ብለዋል።
በበዓሉ አብሮነትና ፍቅርን የሚያንፀባርቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ቁምነገሮችንም ይዟል ነው ያሉት።
የፍቼ ጨምበላላን እሴትን ሀገራችንም ሆነ ዓለም ቢጠቀሙበት የሚያተርፉበት ነው ሲሉ ገልጸው፤ በዓሉን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዓሉ አብሮ የሚበላበት፣ አብሮነት የሚጎላበት፣ ለተፈጥሮ ክብር የሚሰጥበት ድንቅ ባህል የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍቼ ጫምበላላ የዋዜማው በዓል የሆነው ”ፊጣሪ” በተለያዩ ክዋኔዎች ታጅቦ በመከበር ላይ ይገኛል።
በደብሪቱ በዛብህ፣ ብርሃኑ በጋሻው እና አፈወርቅ እያዩ