Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ ዛሬ ማለዳ የመዲናዋ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ለውጥ 6ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ መግለጻቸውን አንስተዋል።

ለውጡ ኢትዮጵያን ከፍ ባደረጉ ታላላቅ ሥራዎች እና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ከፍ ብሎ አንድነት የደመቀበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ደግሞ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጀምረው የተጠናቀቁበት፣ የቱሪዝም መስህቦች እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ የተጀመሩ ለሰው ልጅ ቅድሚያ በሚሰጡ ሰው ተኮር ስራዎች የበርካቶች የኑሮ ሸክም ቀልሎ እምባቸው ታብሶ ተስፋቸው የለመለመበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች በቀጣይ መዲናዋ የብልጽግና ተምሳሌት፣ እንደ ስሟ ውብ እና ለኑሮ ምቹ በማድረግ በሁሉም ዘርፍ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

በዚህም ሁሌም ድጋፋቸው ላልተለየ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አክብሮታችው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው ፥አመስግነዋል።

Exit mobile version