አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት መስጠት የጀመረበትን 78ኛ ዓመት አስመልክቶ የመጀመሪያ በረራ ወዳደረገበት ካይሮ በልዩ ዝግጅት በረራ አድርጓል።
አየር መንገዱ በፈረንጆቹ 1946 መጋቢት 29 በአሥመራ በኩል በማድረግ ወደ ግብጽ ካይሮ በ/5C-47/ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉ ይታወሳል።
ትናንት ምሽት በተደረገው ልዩ ጉዞም የአየርመንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻና ሌሎችም የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ አየር መንገዱ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ የብራንድ አምባሳደር ከመሆን አልፎ የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ ነው።
የአየር መንገዱ የስኬት ምንጭ ደንበኞቹ መሆናቸውን ገልጸው÷በዕለቱ በአየር መንገዱ እየተገለገሉ ላሉ መንገደኞች ስጦታ በመስጠት ማመስገናቸውን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል፡፡