Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ ነው – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የክልሉ የሰላም ሁኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ ነው ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)÷ ህዝብ በሸኔ የሽብር ቡድን ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ሲደርሱበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ የተነሳም ሰላም የህዝቡ ቀዳሚ ጥያቄው ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

የጸጥታ ሀይሉ ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህንን ተከትሎም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት እየተማረኩ እና በሰላም እጃቸውን እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት እየወሰዱ በሚገኙት እርምጃ የጸጥታ ሁኔታው በመሻሻሉ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች እና ፕሮጀክቶች ዳግም መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

እጃቸውን በሰላም እየሰጡ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላትን ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

ከህዝቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶችም በቡድኑ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህዝቡ ጠይቆናል ነው ያሉት።

በቀጣይም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ እጃቸውን በሰላም የሚሰጡትን ተቀብሎ የተሃድሶ ስልጠና መስጠት እና የልማት ስራዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ቢቂላ (ዶ/ር) አመልክተዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version